በኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን እና በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲቲዩት መካከል የአትሌት ባዮሎጂካል ፓስፖርት ላብራቶሪ (ABP) ለማቋቋም የመግባቢያ ሰነድ የፊርማ ስነ-ስርዓት ተካሄደ
***
ታህሳስ 20/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን አበረታች ቅመሞችን (Doping) ለመቆጣጠር የተለያዩ የቁጥጥር ስርዓቶችን በመዘርጋት እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ቆይቷል። ከቁጥጥር ስርዓቶቹ መካከል የአበረታች ቅመሞች ምርመራ አንዱ እና ዋነኛው ሲሆን የሽንት እና የደም ናሙናዎችን ከስፖርተኞች በመሰብሰብ ከአገር ውጪ ወደሚገኙ የምርመራ ላብራቶሪዎች በተለይም ወደ ኳታርና ኬኒያ በመላክ ምርመራውን ሲያካሂድ ቆይቷል።

ይሁን እንጂ ናሙናዎችን ለማጓጓዝ ለ1 (አንድ) ኪሎ ግራም በአማካይ እስከ 150 (መቶ ሀምሳ) የአሜሪካ ዶላር (USD) እና ለምርመራ ለደም ናሙና በአማካይ ከ40 – 60 የአሜሪካ ዶላር (USD)፤ ለሽንት ናሙና በአማካይ ለአንድ ናሙና ከ120 – 400 የአሜሪካ ዶላር (USD) በውጭ ምንዛሬ የሚከፈል በመሆኑ አሁን ካለው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር ተያይዞ የምርመራ መጠኑን በሚፈለገው ደረጃ ማሳደግ አልተቻለም።
በዚህም መሠረት ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ችግሩን በመረዳት ከኢትዮጵያ የማሕበረሰብ ጤና ኢኒስቲቲዩት ጋር የአትሌት ባዮሎጂካል ፓስፖርት የምርመራ ላብራቶሪ ለማቋቋም የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ከቆየ በኋላ ከዓለም-አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ(WADA) የመጀመሪያ ደረጃ እውቅና ማግኘት እና የምርመራ ላብራቶሪው ስራ እንዲጀምር ፈቃድ ተሰጥቷል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ የማህበረሰብ ጤና ኢኒስቲቲዩት የሁለቱም ተቋማት አመራሮች በተገኙበት የመግባቢያ ሰነድ የፊርማ ስነ-ስርዓት የተካሄደ ሲሆን በዝግጅቱ መክፈቻ የኢኒስቲቲዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ “የምርመራ ላብራቶሪው አገራዊ እና ማህበራዊ ፋይዳው በተለይም ለስፖረት ልማት በጣም ከፍተኛ ነው።” ብለዋል። በተጨማሪም ዋና ዳይሬክተሩ ኢኒስቲቲዩቱ ጥራት ያለው እና ደረጃውን የጠበቀ የምርመራ አገልግሎት ለመስጠት በቁርጠኝነት እንደተዘጋጀ ገልፀዋል።

በመቀጠልም የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር አክሊሉ አዛዥ፤ ባለስልጣን መ/ቤቱ ባለፉት 7 (ሰባት) ዓመታት አበረታች ቅመሞችን ለመከላከል እና የዜጎችን ጤና ለመጠበቅ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በጋራ ሲሰራ እንደነበር እና ከነዚህም መካከል አንዱ ኢኒስቲቲዩቱ እንደነበር ገልፀው ባለስልጣን መ/ቤቱ በዓለም-አቀፍ ደረጃዎች እና የአሠራር ስርዓቶች (Code Compliance) መሠረት በትክክል ስራዎችን እያከናወነ መሆኑ ክትትል የሚደረግበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የቦርድ ሰብሳቢው አክለውም ከዚህ ቀደም ምርመራ ለማካሄድ የተለያዩ እንግልቶች እና የውጭ ምንዛሬ ችግር አንደነበር ገልፀው፤ ይህ ላብራቶሪ ከተቋቋመ በኋላ እነዚህ ችግሮች እንደማይከሰቱ እና ላብራቶሪው ለአገራችን ባለሙያዎች እድገት እንደሚጠቅም፤ ለሌሎች አገራትም ምርመራ በማካሄድ የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስገኝ፤ መረጃዎችንም በቀላሉ ለመለዋወጥ እንደሚያስችል፤ ለምርምር ስራዎችን እገዛው ከፍ ያለ እንደሆነ እና ለውጤት አስተዳደር ሥራ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አፅእኖት ሰጥተው አብራርተዋል።

በመጨረሻም የምርመራ ላብራቶሪውን ለማቋቋም የነበረውን ሂደት የሚያሳይ ማብራሪያ እና ገለፃ በአቶ ፈይሰል የሪፈራልና ሪፈረንስ መሪ ሥራ-አስፈፃሚ ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ የፊርማ ስነ-ስርዓቱን በማካሄድ ዝግጅቱ ተጠናቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *