የህግ ጥሰት በፈፀሙ አትሌቶች ላይ የሚተላለፉ ቅጣቶች አገራችን በዓለም-አቀፍ ስፖርት ያላትን ተሳትፎ ማስቀጠልን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸው ተገለፀ

ሚያዚያ 6፣ 2018 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ

በኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን መሥሪያ ቤት እና በመቻል ስፖርት ክለብ አመራሮች መካከል የፀረ-አበረታች ቅመሞች እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ውይይት ተካሂዷል።

ባለስልጣን መ/ቤቱን ወክለው ውይይቱን ያደረጉት አቶ መኮንን ይደርሳል (ዋና ዳይሬክተር) መቻል ስፖርት ክለብ ታሪካዊ የስፖርት ክለብ፣ ዘመናዊ ስፖርትን በማስፋፋት ረገድ ፈር ቀዳጅ የሆነ፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በስፋት የሚሳተፉበት እና ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍና ውክልና ያለው ክለብ እንደሆነ ገልፀው፣ ክለቡን ወክለው የሚወዳደሩ ስፖርተኞች መከላከያ ሠራዊቱንና አገርን ወክለው የሚወዳደሩ በመሆናቸው ክለቡን ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፣ የአበረታች ቅመሞች ጉዳይ በስፖርቱና በስፖርተኞች ላይ አሉታዊ ተፀዕኖው ከፈተኛ እንደሆነ፣ ከዚህም ባሻገር ከፍትኃዊ የስፖርት ውድድር መርህ ጋር የሚጣረስ፤ ዜጎችን ውስብስብ ለሆነ የጤና እክል የሚዳርግ፤ አገራችን በስፖርቱ የገነባችውን በጎ ስም የሚያጠለሽ እና ዙሪያ መለስ የሆነ ሰፊ ጉዳት የሚያስከትል እንደሆነ አብራርተው፣ መንግስት የጉዳዩን አሳሳቢነት በውል በመገንዘብ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ አበረታች ቅመሞችን የመከላከልና የመቆጣጠር ስልጣን ተሰጥቶት በአዋጅ እንዲቋቋም እንዳደረገ ገልፀዋል። በዚህም አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገብ እንደተቻለ እና አገራችን በዓለም-አቀፍ ደረጃ በስፖርቱ የነበራትን ተሳትፎ ለማስቀጠል እንደተቻለ አሳውቀዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አበረታች ቅመሞችን መከላከል የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ኃላፊነት ብቻ እንዳልሆነ፤ ሁሉም አካላት አበረታች ቅመሞች እንቅስቃሴዎችን የመደገፍ ኃላፊነት እንዳለባቸው፤  በተለይ የስፖርት ክለባት ኃላፊነት ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል። በዚህ ረገድ ክለቡ ስፖርተኞችና ድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎች የፀረ-አበረታች ቅመሞች ህጎችንና አሠራሮችን አክብረው እንዲሠሩ የማድረግ፤ ስለ አበረታች ቅመሞችና ዘዴዎች ያላቸውን ግንዛቤ የሚያሳድጉባቸውን መድረኮች የማመቻቸት፣ ስፖርተኞች ራሳቸውን ለ24 ሰዓት ለአበረታች ቅመሞች ምርመራ ዝግጁ እንዲያደርጉ የማሳሰብ፤ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ለሚጠይቃቸው ማንኛውም ህጋዊ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሾችን የመስጠት፤ የፀረ-አበረታች ቅመሞች የህግ ጥሰት ፈፅመው በእገዳ ላይ ከሚገኙ አትሌቶች ጋር ሙሉ ለሙሉ ግንኙነቶችን የማቋረጥ እና ከባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ጋር በቅንጅት ስራዎችን የማከናወን ኃላፊነቶች እንዳሉበት አሳስበዋል። በተለይም የህግ ጥሰት በፈፀሙ አትሌቶች ላይ የሚተላለፉ ማንኛውም ዓይነት ቅጣቶች አገራችን በዓለም-አቀፍ ስፖርት ያላትን ተሳትፎ ማስቀጠልን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውንና ከዚህ ውጪ ሌላ ዓላማ እንደሌላቸው መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

የክለቡ ሥራ-አስፈፃሚ የሆኑት ብርጋዲየር ጀኔራል ኑሩ ሙዘይን በበኩላቸው፣ ክለቡ በህግ ጥሰት ምክንያት ቅጣት ከተጣለባቸው አትሌቶች ጋር ያለውን ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ እንዳቋረጠ እና በቀጣይም መሰል ጉዳዮችን ፈፅመው በሚገኙት ላይ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ህግን ተፈፃሚ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀው፣ ከዚህ ጋር በተያያዘ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እንደሚዘጋጁ፤ ከመረጃ ልውውጥ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ክፍተቶች መፈታት እንዳለባቸው እና ብዥታዎችን የማጥራት ሥራዎች መከናወን እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በመጨረሻም ውይይቱ በሀለቱም ወገን ከሚገኙ የውይይቱ ተሳታፊዎች በተነሱት ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ የሀሳብ ልውውጦች ተደርገው አበረታች ቅመሞችንና ዘዴዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር ዙሪያ ያለውን እንቅስቃሴ በጋራ መደገፍ እና ማጠናከር እንደሚያስፈልግ መግባባት ላይ በመድረስ ተጠናቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *