የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ከፌደራል፣ ከክልል እና ከተማ አስተዳደር የስፖርት ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር እና የስልጠና መድረክ ማካሄድ ጀመረ
ሰኔ 23/2018 ዓ.ም
አዳማ
*********************
በሀገራችን አበረታች ቅመሞችንና ዘዴዎችን ለመከላከል እንዲሁም ለመቆጣጠር ዘርፈ ብዙ ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ። በተለይም የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን በአዋጅ በተሰጠው ስልጣንና ተግባር መሠረት፣ አበረታች ቅመሞችን የመከላከል እና የመቆጣጠር እንዲሁም ከሚመለከታቸው ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የመስራት ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ነው።

የፀረ-አበረታች ቅመሞች እንቅስቃሴ ውጤታማነት ጉዳዩን በባለቤትነት ስሜት ይዘው በሚንቀሳቀሱ የተለያዩ አካላት ትብብር ላይ የሚወሰን በመሆኑ፣ ባለስልጣን መ/ቤቱ ይህንን አስፈላጊነት በመገንዘብ ከተለያዩ ዘርፎች ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል።

በዚህም መሠረት ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በአዳማ ከተማ ከፌደራል እና ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደር ከተገኙ የስፖርት ቢሮ፣ ከስልጠና ማዕከላት ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እና የጋራ የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት መገምገሚያ የውይይት መድረክ ማካሄድ ጀምሯል።
በመድረኩ ላይ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉትና መድረኩን በንግግር የከፈቱት የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል፤ ከፌዴራል፣ ከክልል እና ከከተማ መስተዳድሮች የተውጣጡ አመራሮችና ባለሙያዎች የፀረ-አበረታች ቅመሞች እንቅስቃሴን በጋራ ማጠናከር በሚችሉባቸውና የተጀመሩ ሥራዎችን ይበልጥ ማስፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መድረኩ እንደሚያተኩር ገልጸዋል።

መንግስት ለአበረታች ቅመሞች መከላከያና መቆጣጠሪያ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በአዋጅና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደረጃ በቂ የሕግ ማዕቀፎች መዘጋጀታቸውንና ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት በፌዴራል ደረጃ መፈጠሩን አስታውቀዋል። አክለውም እነዚህ የወጡ ሕጎች በአግባቡ ተግባራዊ መሆንና መፈጸም እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

በትምህርትና ስልጠና ዘርፍም ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን የገለጹት አቶ መኮንን፣ ዜጎች ገና ከትምህርት ቤት ጀምሮ አስፈላጊውን እውቀትና ግንዛቤ ኖሯቸው እንዲወጡ ለማድረግ ጉዳዩ በትምህርት ካሪኩለም (ስርዓተ ትምህርት) ውስጥ እንዲካተት ተደርጎ በየደረጃው ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ክቡር ዳይሬክተሩ አሳውቀዋል።

ከቁጥጥርና ሕግ ማስከበር አኳያ ከአትሌቶች ጀርባ ሆነው የሕግ ጥሰት በሚፈጽሙ አካላት ላይ ተገቢው ክትትል እየተደረገ አስተዳደራዊ እርምጃዎች እየተወሰዱ ከመሆኑም ባለፈ የወንጀል ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የአበረታች ቅመም ሕግ ጥሰት በስፖርቱ ዘርፍ ላይ ብቻ ሳይሆን የዜጎችን ጤና አደጋ ላይ የሚጥልና የሀገርን ገጽታ የሚያጠለሽ በመሆኑ፣ ጥሰቱን የሚፈጽሙ አካላት በወንጀል ጭምር እንደሚጠየቁ አሳስበዋል። ችግሩን ከጅምሩ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሰፊ ርብርብ ሲደረግ መቆየቱንም ክቡር ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልጸዋል።
አበረታች ቅመሞች በስፖርተኞች ጤና፣ በማኅበረሰቡና በሀገር ላይ የሚያስከትሉትን ከፍተኛ ጫና ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በቂ ግንዛቤ በመስጠት ረገድ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተመላክቷል።

የተጀመረው መድረክ በአበረታች ቅመሞች የሕግ አተገባበር፣ በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች እና የውይይት ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ለሚቀጥሉት ቀናት የሚቆይ ይሆናል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *