የፀረ-አበረታች ቅመሞች የህግ ጥሰት በፈፀሙ አትሌቶች ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈባቸው
የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን የምርመራና ቁጥጥር ተግባሩን በተጠናከረ መልኩ በማከናወን የህግ ጥሰት ፈፅመው በተገኙ አካላት ላይ በአገር-አቀፍ እና ዓለም-አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ህግ መሠረት አግባብነት ያለው የቅጣት እርምጃ እንዲወሰድ የማድረግ ኃላፊነት ያለበት መሆኑ ይታወቃል። በዚህም መሠረት አትሌት አስቻለው አለምነው ደጉ እና አትሌት ናኦል ገመቹ ደምሹ የፀረ-አበረታች ቅመሞች የህግ-ጥሰት ፈፅመው መገኘታቸው በመረጋገጡ በኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን የመጀመሪያ ዳኝነት ሰሚ የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።
የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ተገቢውን የአሠራር ሥርዓት በመከተል አትሌት አስቻለው አለምነው ደጉ እና አትሌት አትሌት ናኦል ገመቹ ደምሹ የተከለከሉ አበረታች ቅመሞችን ወይም ዶፒንግ በመጠቀማቸው የህግ ጥሰት የፈፀሙ መሆናቸው አረጋግጧል።
በዚሁ መሠረት አትሌት አስቻለው አለምነው ደጉ እ.ኤ.አ ጥር 15/2026 በተካሄደው የናሙና ምርመራ ኤሪትሮፖቲን (Erythropoietin (EPO)) የተባለውን የተከለከለ ንጥረ ነገር መጠቀሙ በመረጋገጡ እ.ኤ.አ ከግንቦት 28/2026 – ግንቦት 27/2030 በማንኛውም የስፖርት ውድድር ላይ እንዳይሳተፍ ለአራት (4) ዓመታት የሚፀና እገዳ ተጥሎበታል፡፡ በተጨማሪም አትሌቱ እ.ኤ.አ ከጥር 15/2026 ጀምሮ ያስመዘገበቻቸው ማናቸውም የውድድር ውጤቶች ተሰርዘዋል፤ ይህም ሜዳሊያዎችን፣ የማዕረግ ስሞችን፣ ነጥቦችን እና የሽልማት ገንዘቦችን መመለስን ይጨምራል ።
በተመሳሳይአትሌት ናኦል ገመቹ ደምሹ እ.ኤ.አ ጥር 15/2026 በተካሄደው የናሙና ምርመራ ኤሪትሮፖቲን (Erythropoietin (EPO)) የተባለውን የተከለከለ ንጥረ ነገር መጠቀሙ በመረጋገጡ እ.ኤ.አ ከጥር 28 /2026 – ጥር 27/2030 በማንኛውም የስፖርት ውድድር ላይ እንዳይሳተፍ ለአራት (4) ዓመታት የሚፀና እገዳ ተጥሎበታል፡፡ በተጨማሪም አትሌቱ እ.ኤ.አ. ከጥር 15/2026 ጀምሮ ያስመዘገበቻቸው ማናቸውም የውድድር ውጤቶች ተሰርዘዋል፤ ይህም ሜዳሊያዎችን፣ የማዕረግ ስሞችን፣ ነጥቦችን እና የሽልማት ገንዘቦችን መመለስን ይጨምራል ።
በቀጣይም በሀገራችን በየደረጃው የሚደረገው የምርመራና ቁጥጥር ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን የስፖርት አበረታች ቅመሞችን በመጠቀምም ይሁን በተለያየ መልኩ የፀረ-አበረታች ቅመሞች የህግ ጥሰት በሚፈፅሙ አትሌቶችና ከጀርባ ሆነው በሚተባበሩ ሌሎችም ግለሰቦች ላይ የሚወስደውን የእርምት እርምጃ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ለማሳወቅ ይወዳል፡፡

