“የአበረታች ቅመም የምርመራ ስራ አሁን ላይ ከሚገኝበት የአፈፃፀም ደረጃ አንፃር በአህጉር አቀፍ ደረጃ ለሚገኙ ተመሳሳይ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ተቋማት አጋዥ ወደ መሆን መሸጋገር ይኖርበታል!” አቶ መኮንን ይደረሳል

የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን በዛሬው ዕለት ለአበረታች ቅመሞች (ዶፒንግ) ናሙና ሰብሳቢ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጥቷል። በመድረኩ ተገኝተው ስልጠናውን በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩት የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል እንደገለፁት፤ በዓለም-አቀፍ ደረጃ በሚገኙ በሁሉም የፀረ-አበረታች ቅመሞች ተቋማት እየተካሄደ የሚገኘው የናሙና አሰባሰብ ሂደት ተመሳሳይ እና ወጥነት ያለው የአሰራር ስርዓትን የሚከተል በመሆኑ፣ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ፣ እነዚህን የአሰራር ስርዓቶች በጠበቀ መልኩ ስራዎችን ሲያከናውን እንደቀየ፤ ለዚህም ሲባል ለናሙና ሰብሳቢ ባለሙያዎች በየጊዜው ተደጋጋሚ ስልጠናዎች እየተሰጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል። በተጨማሪም ከአበረታች ቅመሞች የናሙና  አሰባሰብ ሂደት ጋር በተገናኘ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በየጊዜው የተለያዩ ስልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረው፣ የሚዘጋጁት ስልጠናዎች ራስን ለማብቃት እንደ ግብዓት ተወስደው ተከታታይነት ባላው ንባብ እና ልምምድ ሊዳብሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከአበረታች ቅመሞች ምርመራና ቁጥጥር ጋር በተገናኘ የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ አፈፃፀም በየጊዜው እየተሻሻለ እንደሚገኝ ገልፀው፤ የምርመራ ሥራው አሁን ከሚገኝበት የአፈፃፀም ደረጃ አንፃር ከአገር ውስጥ የምርመራ ሥራዎች ባሻገር በአህጉር አቀፍ ደረጃ ለሚገኙ አቻ ተቋማት እገዛ ወደ ማድረግ መሸጋገር ይኖርበታል ብለዋል።

ስልጠናው በሙያው የረጅም ዓመታት ልምድ ባላቸው የዓለም አትሌቲክስ የአበረታች ቅመሞች የምርመራ ቡድን ከውድድር ጊዜ ውጪ ምርመራ አስተባባሪ በሆኑት ተጋባዥ አሠልጣኝ ወ/ሮ ጃስሚና ጀሲካ በንድፈ ሃሳብ እና በተግባር የተሰጠ ሲኾን፤ በአጠቃላይ ዝግጅቱ አዳዲስ እና የተሻሻሉ የአሠራር ስርዓቶችን ጨምሮ የሽንትና የደም ናሙና አሰባሰብን የተመለከቱ ልዩ ልዩ የስልጠና ርዕሶች ተካተውበት ተካሂዷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *