አትሌት ድርቤ ወልተጂ ቀደም ሲል በፈፀመችው የፀረ-አበረታች ቅመሞች የሕግ ጥሰት ጥፍተኛ በመባሏ አስተዳደራዊ ቅጣት ተጣለባት።

የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን የምርመራ ባለሞያዎች (Sample Collection Personnel) እ.ኤ.አ የካቲት 25/2025 በአትሌቷ ላይ የአበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ ምርመራ ለማካሄድ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ፈቃደኛ ባለመሆኗ ሳይሳካ የቀረ መሆኑ ይታወሳል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ አትሌት ድርቤ ወልተጅ የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ህግ አንቀፅ 2.3 በመተላለፍ ተጠርጥራ ጉዳዩ ለአለም አቀፉ የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት(CAS) ይግባኝ የቀረበ ሲሆን ላለፉት አምስት ወራትም ጉዳዩ በፍ/ቤቱ ሲታይ ቆይቷል። በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ የቀረቡትን የክርክር ኃሳቦች እና ማስረጃዎች በጥልቀት ከመረመረ በኋላ አትሌቷ ጥፋተኛ መሆኗን በማረጋገጥ ውሳኔ አስተላልፏል።

በዚህም መሰረት አትሌት ድርቤ ወልተጂ እ.ኤ.አ ከሐምሌ 08/2025 ጀምሮ እስከ ሰኔ 30/2027 ዓ.ም ለሁለት ዓመታት በማንኛውም ስፖርታዊ ውድድር ላይ እንዳትሳተፍ እገዳ ተጥሎባታል። በተጨማሪም ፍ/ቤቱ እ.ኤ.አ ከየካቲት 25/2025 ዓ.ም ጀምሮ በተካሄዱ የተለያዩ ውድድሮች ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች (ሜዳሊያ፣ ሽልማት፣ ደረጃ) ሁሉ እንዲሰረዙ ወስኗል።

የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን በቀጣይም ንፁህ ስፖርት ለማስፋፋት እና ህግን ለማስከበር በቂ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ መሆኑን እያረጋገጠ አትሌቶች ከእንደዚህ አይነት መሰል ጥፋቶች እንዲቆጠቡ ጥሪውን ያስተላልፋል። በተለይም የአትሌት ቤተሰቦችና ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞች በፀረ-አበረታች ቅመሞች እንቅስቃሴ ውስጥ ጣልቃ በመግባት ሂደቱን ከማወክ እና ከማስተጓጎል እንዲታቀቡ ያሳስባል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *