“የፋርማሲው ሴክተር መደሃኒቶችን ለታለመላቸው ዓላማ ብቻ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ማድረግ ይጠበቅበታል።”
አቶ መኮንን ይደርሳል
መጋቢት 23/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ

የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ፋርማሲ ማህበር ጋር በመቀናጀት ለማህበሩ አባላት በፀረ-አበረታች ቅመሞች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል ።
በስልጠናው መክፈቻ መድረኩን በንግግር የከፈቱት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ መኮንን ይደርሳል፡-ከዚህ ቀደም የፋርማሲውን ዘርፍ በቅርበት ለማወያየት እንደተሞከረ፣ ከማህበሩ አመራሮች ጋር በቅንጅት የተለያዩ ሥራዎች እንደተከናወኑ እና የጋራ የውይይት መድረኮች ተዘጋጅተው ለውጥ የታየባቸው አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን ገልፀዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ከመቋቋሙ በፊት በአገራችን እና በስፖርቱ ላይ ተደቅነው የነበሩ አደጋዎችን በአጭር ጊዜ በመለወጥ አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገብ እንደተቻለ ጠቁመው፣ በተለይ በአለም አቀፍ መድረክ እንድንታይ እና ስማችን ከፍ ብሎ እንዲጠራ ያደረገን ስፖርት ለሀገራችን ትልቅ ትርጉምና ፋይዳ ያለው በመሆኑ ስፖርተኞች ተፈጥርአዊ በሆነ መንገድ በሚያገኙት ስልጠና ላይ ተመስርተው ዉጤት እንዲያገኙ በጋራ መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የአበረታች ቅመሞች /ዶፒንግ/ ጉዳይ ስፖርቱን ብቻ የሚመለከት ጉዳይ እንዳልሆነና በዜጎች ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ የፋርማሲው ሴክተር መደሃኒቶችን ለታለመላቸው ዓላማ ብቻ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ማድረግ ይጠበቅበታል።” በማለት አሳስበዋል።
ስልጠናው Anti-doping and Sport Drugs፡ Role of Pharmacists በሚል ርዕስ በአቶ ሰለሞን አሰፋ ፋርማኮሎጂስት እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ተሰጥቷል። በመቀጠልም Overview of Professional Ethics and Professionalism እና የፀረ-አበረታች ቅመሞች የሕግ ጥሰት ሁኔታ፣ እንድምታና ከፋርማሲስቶች የሚጠበቀው ሚና በሚሉ የስልጠና ርዕሶች በአቶ አሰግድ በቀለ ከጤና ሚኒስቴር ተጋባዥ እንግዳ እና በአቶ ንጋቱ መኮንን ከኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን የውጤት አስተዳደር እና ህግ ትግበራ መሪ ሥራ-አስፈፃሚ በቅደም ተከተል ተሰጥቷል።
ከስልጠናው ተሳታፊዎች በቀረቡት የስልጠና ርዕሶች ዙሪያ የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው በአሰልጣኞች ሰፊ ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቶባቸው መርሀ-ግብሩ ተጠናቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *