“ክለቦች የፀረ-አበረታች ቅመሞች እንቅስቃሴ ባለድርሻ አካል ሳይሆኑ የጉዳዩ ዋና ባለቤት ናቸው።” አቶ መኮንን ይደርሳል

ጥቅምት 26/2019 ዓ.ም (አዲስ አበባ)

የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን የስፖርቱን ንፅህና እና ፍትሃዊነት የመጠበቅ ተልዕኮውን ለማሳካት፤ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት የስፖርት ልማትንና ጥራትን የማስፋፋት፣ የስፖርተኞችን ደህንነት የመጠበቅ እና የግንዛቤ ማሳደግ አቅምን የማጠናከር ዘርፈ-ብዙ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል።

በዚሁ መሠረት ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ከአዲስ አበባ አትሌቲክስ ክለባት አመራሮች እና አሰልጣኞች ጋር በስፖርት አበረታች ቅመሞች እና በህግ ማዕቀፎች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የውይይት መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይረክተር አቶ መኮንን ይደርሳል ባስተላለፉት መልእክት፤ መንግስት አበረታች ቅመሞችን የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም የስፖርት ፖሊሲ፣ የወንጀል ህግ እና የስፖርት አስተዳደር አዋጅን ጨምሮ በቂ የህግ ማዕቀፎች ወጥተው ወደ ትግበራ መግባታቸውን አብራርተዋል። ከምንም በላይ ደግሞ የህግ ጥሰት የሚፈፅሙ አካላትን በመለየት አስተማሪ የሆኑ የእርምት እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

አትሌቲክስ ክለቦች ለስፖርቱ በቂ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እና በስነምግባር የታነጹ ንጹህ አትሌቶችን ሊያፈሩ እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል። በተለይም ክለቦች የፀረ-አበረታች ቅመሞች እንቅስቃሴ ባለድርሻ አካል ሳይሆኑ የጉዳዩ ዋና ባለቤት መሆናቸውን አብራርተዋል።

ስፖርቱን ማልማት የጋራ ኃላፊነት እንደሆነ የገለጹት አቶ መኮንን፤ አትሌቶች በውድድር ውጤታቸው ብቻ ሳይሆን በስነምግባር እና በንጽህናቸው ሊመዘኑ እንደሚገባ አፅዕኖት ሰጥተው ገልፀዋል። አበረታች ቅመም የሀገርን ስም የሚያጠለሽ እና በንጹህ ስፖርት የተወዳደሩ የቀደምት አትሌቶችን ታሪክ የሚያበላሽ ተግባር በመሆኑ ሁላችንም የጋራ ኃላፊነታችንን ልንወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በቀረቡት የስልጠና ርዕሶች እና አጠቃላይ በፀረ-አበረታች ቅመሞች እንቅስቃሴ ዙሪያ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ተሰንዝረው በወቅቱ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር ስለሺ ስህን እና በዋና ዳይሬክተሩ ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

በመጨረሻም  ዋና ዳይሬክተሩ ፕሮግራሙን ሲያጠቃልሉ ክለቦች በቀጣይ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩባቸው የሚገቡ ዋና ዋና ነጥቦችን በሚከተለው መልኩ አስቀምጠዋል፦
የመረጃ አያያዝ፦ ክለቦች የአትሌቶቻቸውን የተሟላ መረጃ በጥንቃቄ ለይተው መመዝገብ እና አደራጅተው መያዝ እንዳለባቸው፤

የስልጠና ይዘት፦ የዶፒንግን ጉዳይ በስልጠና ማንዋሎቻቸው ውስጥ ማካተት እንደሚገባቸው፤

የባህሪ እና የስነምግባር ግንባታ፦ አትሌቶች የባህሪ ለውጥ እንዲያመጡ እና በስነምግባር የታነጹ እንዲሆኑ መስራት፤

የውስጥ መመሪያዎች፦ ክለቦች የራሳቸው የውስጥ መመሪያ እና ደንብ ሊኖራቸው እንደሚገባ እና አትሌቶችም እነዚህን ህጎችና አሰራሮች አክብረው መሄድ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *