በአገራችን አበረታች ቅመሞችን ወይም ዶፒንግን ለመከላከልና ለመቆጣጠር መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ ተገለፀ
በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በጋራ በመሆን ከኤሊት ስፖርተኞች፣ ከአሰልጣኞች፣ ከማናጀሮችና ከተወካዮች ጋር በአበረታች ቅመሞች መሰረታዊ ጉዳዮች እና በህግ ማዕቀፎች ዙሪያ ውጤታማ የውይይት መድረክ አካሂደዋል፡፡ በዚህ የውይይት መድረክ ላይ መንግስት በአገራችን አበረታች ቅመሞችን ወይም ዶፒንግን በዘላቂነት በመከላከልና በመቆጣጠር ንፁህ ስፖርት ለማስፋፋት በተለይም አትሌቲክሱን ጠብቆ በማቆየት የአገር ክብርነቱን ለማስቀጠል መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑ ተመላክቷል፡፡ የስፖርት ፖሊሲውን፣ የወንጀል ህጉንና የስፖርት አስተዳደር አዋጁን ጨምሮ በቂ የሆኑ የህግ ማዕቀፎች ወጥተው ወደ ትግበራ መግባታቸው፣ በየደረጃው የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫና የህዝብ ንቅናቄ ተግባራት ተቀርፀው በመከናወን ላይ መሆናቸው፤ ከምንም በላይ ደግሞ የህግ ጥሰት የሚፈፅሙ አካላትን በመለየት አስተማሪ የሆኑ የእርምት እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡ ባለፈው ጊዜ በተካሄደው እንቅስቃሴም እጅግ በጣም አንፀባራቂ ውጤቶች መመዝገባቸው ተመላክቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ2026 በየደረጃው በተካሄዱ ምርመራዎች 20 የሚሆኑ አትሌቶች በተለያየ መልኩ የአበረታች ቅመሞች የህግ ጥሰት መፈፀማቸው በመረጋገጡ እንደየ ጥፋታቸው መጠን የተለያዩ የቅጣት ውሳኔዎ መተላለፋቸው የተገለፀ ሲሆን ከአትሌቶች ጀርባ በመሆን በህግ ጥሰቱ ውስጥ የተሳተፉ የተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማትም ተጠያቂ መደረጋቸውን በመድረኩ ላይ ተገለጧል፡፡ በቀጣይም መንግስት በአበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ ላይ ያለው አቋም እጅግ በጣም ጠንካራ መሆኑንና የወንጀል ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ስራም በትኩረት እንደሚሰራ በኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ተገልጧል፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር በሰጡት ማጠቃለያ አትሌቲክስ በአለም አቀፍ መድረክ ከፍ የሚያደርገን የአገር ኃብት እና ትውልድ የሚገነባበት መሳሪያ መሆኑን አመላክተው ልንከባከበውና ንፅህናውን ጠብቀን ለቀጣዩ ትውልድም ልናስተላልፈው ይገባል ብለዋል፡፡ ለዚህም አትሌቱና የስፖርቱ ሙያተኛ የማይተካ ሚና እንዳለው የገለፁ ሲሆን በተለይም ራሳቸውን ንፁህ በማድረግ ሌሎችም ወደ አበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ የህግ ጥሰት እንዳይገቡ መከላከል የሚጠበቅባቸው መሆኑን አሳስበዋል፡፡
በቀጣይም አበረታች ቅመሞችን ወይም ዶፒንግን በዘላቂነት በመከላከልና በመቆጣጠር የአገራችንን መልካም ገፅታ ለማስጠበቅ እና የስፖርት ዲፕሎማሲ ግባችንን ለማሳካት እቅድ ተይዞ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተገልጧል፡፡ ይህ መድረክም የዚህ ስራ አካል ነው ተብሏል፡፡
**********
መስፈንጠሪያውን በመጫን የማህበራዊ ትስስር ገፆቻችን ይቀላቀሉ፤ ይከታተሉ፤ ይወዳጁ
ቲክቶክ፡- tiktok.com/@eth_ada1
ፌስቡክ፡- facebook.com/ETHNADO
ኤክስ (ቲዊተር)፡- x.com/eadaantidoping
ቴሌግራም፡- t.me/EthiopianADA
ዩቱዩብ፡- youtube.com/@EthiopianAnti-DopingAuthority
ድረ-ገፅ፡- ethada.org.et

