በአዲስ አበባ ከተማ በሁሉም ክፍለ-ከተሞች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለሚያስተምሩ የሰውነት ማጎልመሻ መምህራን የፀረ-አበረታች ቅመሞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ!
ጥቅምት 29/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ ፀረ አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ እና በአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በትብብር በተዘጋጀው የአቅም ግንባታ ስልጠና በሁሉም ክፍለ ከተማ ለሚገኙ የሰውነት ማጎልመሻ መምህራን በሁለት ቡድን የፀረ-አበረታች ቅመሞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል።
ስልጠናው በቡድን 1 ከየካ፣ ቦሌ፣ ለሚኩራ፣ አራዳ እና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ለመጡ ሰልጣኞች በአቶ ፈለቀ ዋለልኝ አማረ የአበረታች ቅመሞች መከላከል፣ ግንዛቤ እና የህዝብ ንቅናቄ መሪ ሥራ-አስፈፃሚ የተሠጠ ሲሆን፤ በአቶ መንግስቱ የምሩ ስሜ የአበረታች ቅመሞች ኢንተለጀንስ እና ኢንቨስቲጌሽን መሪ ሥራ-አስፈፃሚ እና በወ/ሮ ፍሬህይወት እሱባለው የፀረ-አበረታች ቅመሞች ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ በቡድን 2 ከጉለሌ፣ ኮልፌ፣ ልደታ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ አዲስ ከተማ እና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ-ከተማ ለመጡ ሰልጣኞች ተሰጥቷል።
የስልጠናው ይዘት በአበረታች ቅመሞች ምንነት (ፅንሰ-ሀሳብ) ፣ የፀረ-አበረታች ቅመሞች የህግ ጥሰቶች፣ አበረታች ቅመሞች የሚያስከትሏቸው ጉዳቶች፣ የፀረ-አበረታች ቅመሞች አሠራር ስርዓቶች እና በአበረታች ቅመሞች ምርመራና ቁጥጥር ሂደት ዙሪያ ትኩረት ያደረገ ነው።
ከሰልጣኞች ስለ አበረታች ቅመሞች የመገኛ አድረሻ፣ የስፖርት ድጋፍ ሰጪ ምግቦች (Supplements)፣ በአበረታች ቅመሞች ናሙና አሰባሰብ ሂደት እና መሰል በስልጠናው ይዘት ዙሪያ ለተነሱ ጥያቄዎች በአሰልጣኞች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

