አትሌት ገመኔ ማሚቴ ቱኑኩ የተከለከለ አበረታች ቅመም ወይም ዶፒንግ ተጠቅማ መገኘቷ በላብራቶሪ ምርመራ በመረጋገጡ ይፋዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች የህግ ጥሰት የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባታል።
የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን በሁለት የተለያዩ ውድድሮች ላይ ባካሄዳቸው ምርመራዎች አትሌቷ ኤሪትሮፖይቲን (EPO) እና ዴክሳሜታሶን (Dexamethasone) የተሰኙ የተከለከሉ ንጥረ-ነገሮችን መጠቀሟን ማረጋገጥ ችሏል።
በዚህም መሠረት አትሌት ገመኔ ጊዜያዊ እገዳ ከተጣለበት ከህዳር 02/2018 ዓ.ም (November 11, 2025) ጀምሮ ለስድስት (6) ዓመታት የሚፀና በማንኛውም ስፖርታዊ ውድድር እንዳትሳተፍ እገዳ ተጥሎባታል። በተጨማሪም አትሌቷ ከግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ.ም (May 11, 2025) ጀምሮ በተካሄዱ የተለያዩ ውድድሮች ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች ሁሉ እንዲሰረዙ ተወስኗል። ይህም ሜዳሊያዎችን፣ የማዕረግ ስሞችን፣ ደረጃዎችን እና የሽልማት ገንዘቦችን መመለስን ይጨምራል።
በቀጣይም በአገራችን በየደረጃው የሚደረገው የምርመራና ቁጥጥር ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን የኢትዮጵያ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን የስፖርት አበረታች ቅመሞችን በመጠቀምም ይሁን በተለያየ መልኩ የፀረ-አበረታች ቅመሞች የህግ ጥሰት በሚፈፅሙ አትሌቶችና ከጀርባ ሆነው በሚተባበሩ ሌሎችም ግለሰቦች ላይ የሚወስደውን የእርምት እርምጃ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ያሳውቃል።
*******
መስፈንጠሪያውን በመጫን የማህበራዊ ትስስር ገፆቻችን ይቀላቀሉ፤ ይከታተሉ፤ ይወዳጁ


