በፍትህ አካላት መካከል የሚታየው የቅንጅት እና የመናበብ ክፍተት የፀረ-አበረታች ቅመሞች ህጎችን በውጤታማነት ለመተግበር ተግዳሮት መሆኑ ተጠቆመ
ሰኔ 3/2018 ዓ.ም፣ አዳማ
*****************
የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ለፍትህ አካላት በዛሬው ዕለት ያዘጋጀው የስልጠናና የውይይት መድረክ በተሳካ ሁኔታ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በውይይቱ በፍትህ አካላት መካከል የሚታየው የቅንጅት እና የመናበብ ክፍተት የፀረ-አበረታች ቅመሞች ህጎችን በውጤታማነት ለመተግበር ተግዳሮት መሆኑን የውይይት መድረክ ተሳታፊዎች ገለፀዋል። ተሳታፊዎቹ ችግሩን ለመቅረፍ የተቀናጀ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት እና ሰፊ የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባ አሳስበዋል።

የፍትህ አካላት ተወካዮች በቀረቡት የውይይት ሰነዶች ላይ በሰጡት አስተያየት፤ ወንጀሉን በጋራ ለመከላከል ተቋማዊ ትስስርን ማጠናከር እና ዘርፉን በቁርጠኝነት ማገዝ እንደሚገባ ጠቁመው በተለይም ስለ አበረታች ቅመሞች (ዶፒንግ) ምንነትና አስከፊነት በየደረጃው ላሉ የህግ አስከባሪዎችና ማህበረሰብ ክፍሎች ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እንደ ቀጣይ አቅጣጫ ሊወሰዱ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በመድረኩ ላይ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የማጠቃለያ ምላሽ የሰጡት የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፋንታዬ ገዛኸኝ፣ ከመድረኩ የተነሱት ገንቢ ሃሳቦች ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት አጋዥ መሆናቸውን ገልጸው በትልቁ የሚስተዋለውን እና በተሳታፊዎች የተነሳውን የግንዛቤ እጥረት ለመቅረፍ በቀጣይ በየክፍለ ከተማው ተደራሽ የሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮችን መዘርጋት የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አስታውቀዋል።

የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት ነባር የህግ ማዕቀፎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተግባራዊ ባልሆኑበት ተጨማሪ የዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ህጎች እየወጡ መሆኑን አስታውሰው፣ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ከመድረኩ የተነሱትን የቅንጅትና የተነሳሽነት ማነስ ችግሮች በአስቸኳይ ማረም እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተው ገልፀዋል። ጉዳዩን በባለቤትነት ስሜት ለመወያየት የሚያስችሉ ቀሪ የቤት ስራዎች ስላሉ፣ የስልጠና እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ በማጠቃለያቸው ላይ እንዳሳሰቡት፤ የሚመለከታቸው አካላት ወደ እነሱ በሚመጡ የአበረታች ቅመሞች ወንጀል መዝገቦች ላይ በከፍተኛ ተነሳሽነትና በሃላፊነት ስሜት ሊሰሩ እንደሚገባ ገልፀዋል።
በመጨረሻም ዋና ዳይሬክተሩ፡- የአበረታች ቅመሞች (ዶፒንግ) ጉዳይ የስፖርት ብቻ ሳይሆን የጤና፣ የኢኮኖሚ፣ የስነ-ልቦና እና የማህበራዊ ቀውስ እንደሆነ እና አልፎም የሀገርን መልካም ገጽታ የሚያበላሽ ከባድ ወንጀል በመሆኑ ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን ተረድተን በጋራ መሥራት እንደሚገባ በመግለፅ መድረኩ ተጠናቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *