የፀረ-አበረታች ቅመሞች የህግ ጥሰቶችን ለመከላከል የፍትህ አካላት በባለቤትነት ስሜት መሥራት እንደሚገባቸው ተገለፀ::
***********************

የአበረታች ቅመሞች በዜጎች ላይ እያሰከተለ የሚገኘው የጤና፣ የስነ ልቦና እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ከፍተኛ በመሆኑ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዎችን የህግ አካላት፣ ፖሊሰ እና ሌሎች የህግ አሰፈጻሚ አካላት በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸው የኢትዮጵያ ጸረ አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ለፍትህ አካላት በተዘጋጀ የፀረ-አበረታች ቅመሞች የስልጠናና የውይይት መድረክ ወቅት ነው፡፡
መድረኩን በአካል ተገኝተው በንግግር የከፈቱት የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር መኮንን ይደርሳል፡- የአበረታች ቅመሞች በዜጎች ላይ እያሰከተለ የሚገኘው የጤና እክል፤ የስነ ልቦና እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ከፍተኛ መሆናቸውን ገልፀው፣ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዶፒንግን ለመከላከል ባለፉት ስምንት አመታት በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል። ከዚህም በተጨማሪ መንግስት ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ትውልድን ከመሰረቱ ለመቅረፅ በሚያግዝ መንገድ የፀረ-አበረታች ቅመሞችን ጉዳይ በመደበኛ የትምህርት ስርዓት ውስጥ እንዲካተት በማድረግ ተማሪዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ ስለ አበረጻች ቅመሞች ጉዳት እና ችግሮች እንዲገነዘቡ ለማድረግ ሰፋፊ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፣ የፀረ-አበረታች ቅመሞች የህግ ጥሰቶችን ለመከላከል የተለያየ ዓለም-አቀፍና ሀገር-አቀፍ የህግ ማዕቀፎች፣ መመሪያዎችና ፖሊሲዎች መኖራቸውን አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም በመንግስት በኩል ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠውን አበረታች ቅመሞችን (ዶፒንግ) የመከላከልና መቆጣጠር እንቅስቃሴ የፍትህ አካላት የህግ ተፈጻሚነት ላይ በባለቤትነት ስሜት ሚናቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ተናግረው ንጹህ ስፖርትን ለማስፋፋት የሚመለከታቸው አካላት በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

መድረኩ በተለያዩ የስልጠናና የውይይት ርዕሶች ቀጥሎ የሚውል ሲሆን፣ በጠዋቱ መርሀ-ግብር ዓለም-አቀፍ የፀረ-አበረታች ቅመሞች የህግ ማዕቀፎችን በሚመለከት በባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የውጤት አስተዳደርና ህግ ጉዳዮች መሪ ሥራ-አስፈፃሚ በሆኑት በአቶ ንጋቱ መኮንን በንደፈ-ሀሳብ ገላፃ እየተደረገ ይገኛል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *