ስፖርት ጋዜጠኞች የአበረታች ቅመሞች (ዶፒንግ) ዘገባዎችን የሙያ ስነ-ምግባርን ባከበረ መልኩ ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለፀ

ግንቦት 27/2018 ዓ.ም

አዳማ

የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ጋር በመተባበር ለስፖርት ጋዜጠኞች በፀረ-አበረታች ቅመሞች (ዶፒንግ) ዙሪያ የስልጠና እና የውይይት መድረክ አካሄደ።

ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የአበረታች ቅመሞች በስፖርቱ ዕድገት ላይ የሚያስከትሉትን ጉዳት በዘላቂነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ልዩ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫና የንቅናቄ ስራዎችን በከፍተኛ ትኩረት እያከናወነ ይገኛል። የንጹህ ስፖርት መርሆዎችንና እሴቶችን ለማጎልበት እንዲሁም በማህበረሰቡ ዘንድ ግንዛቤን ለማስረጽ የተጀመረው የፀረ-አበረታች ቅመሞች የሚዲያ ንቅናቄ ፕሮግራም ከግንቦት 14/2018 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ነው።

በማሰልጠኛ መድረኩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ መኮንን ይደርሳል፤ የስፖርት ጋዜጠኞች በአበረታች ቅመሞች ዙሪያ በስፖርቱ ማህበረሰብና በባለድርሻ አካላት ዘንድ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወን እንደሚችሉ ገልጸዋል። የፀረ-አበረታች ቅመሞች መከላከል ስራ ከሚዲያው እንቅስቃሴ ተለይቶ እንደማይታይም ጠቅሰው፣ በዚህ ረገድ ሚዲያ የማይተካ ሚና እንዳለው አመላክተዋል።
ባለፉት ዓመታት ህብረተሰቡ ዶፒንግን እንዲጸየፍ እና ንጹህ የስፖርት ማህበረሰብ እንዲፈጠር በማድረግ ረገድ የሚዲያ ባለሙያዎች ያበረከቱት አስተዋጽዖ ከፍተኛ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የፀረ-አበረታች ቅመሞች ቁጥጥር ስራ ይበልጥ በሳይንስ እና በቴክኖሎጂ እየታገዘ እንደሚገኝ የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱም ከወቅቱ ጋር በመራመድ ተቋማዊ ብቃቱንና የመፈጸም አቅሙን ለማሳደግ እየሰራ ነው ብለዋል። በተጨማሪም የፀረ-አበረታች ቅመሞች ትምህርት በ ሥርዓተ-ትምህርት ውስጥ እንዲካተት መደረጉና በስፖርት ማዕከላት ተከታታይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸው በዘላቂነት ውጤት እንደሚያመጣ ገልጸዋል።

ባለስልጣኑ የምርምር እና የቁጥጥር አቅሙን እያሳደገ እንደሚገኝና ህገ-ወጥ ተግባር በሚፈጽሙ አትሌቶችም ሆነ ሌሎች አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። የመከላከል እና የመቆጣጠር አቅም ማደግ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተሳትፎ፣ ተወዳዳሪነትና ስኬታማነት ለማስቀጠል እንዲሁም የስፖርቱን ተአማኒነት ለማጽናት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወትም አክለዋል።
በመጨረሻም፣ አበረታች ቅመሞች በዜጎች ላይ የሚያስከትሉት የጤና፣ ማህበራዊ፣ ስነ-ልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ዜጎችን ከዚህ አደጋ የመጠበቅ ኃላፊነት የሁሉም ቢሆንም የሚዲያው ዘርፍ ግን የላቀ ድርሻ እንዳለው አሳስበዋል።
በመድረኩ ላይ በባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የአበረታች ቅመሞች መከላከል፣ ግንዛቤ እና የህዝብ ንቅናቄ መሪ ሥራ አስፈፃሚ በአቶ ፈለቀ ዋለልኝ አማካኝነት፤ የአበረታች ቅመሞች ጽንሰ-ሀሳቦች፣ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የዶፒንግ ተፅዕኖ እንዲሁም የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች እንቅስቃሴን የተመለከቱ ሰነዶች ቀርበዋል። በተመሳሳይ ከኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ነዋይ ይመር ጋር በመተባበር ዶፒንግ እና የጋዜጠኞች የዘገባ ስነ-ምግባርን የተመለከቱ የመወያያ ሰነዶች ቀርበው የምክክርና የጥያቄና መልስ ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *