ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2027 የሚካሄደውን አለም አቀፍ የፀረ-ዶፒንግ ትምህርት ጉባኤ (Global Education Conference) ለማዘጋጀት ተመረጠች።

አገራችን ኢትዮጵያ ለጀመርነው ሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸውን አለም አቀፍ ኩነቶች በብቃት በማዘጋጀት ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ የአለም አቀፉ የፀረ-ዶፒንግ ትምህርትና ስልጠና ጉባኤ (Global Education Conference) በአለም አቀፉ የፀረ-ዶፒንግ ኤጀንሲ (WADA) አዘጋጅነት በየጊዜው በመካሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን አገራችን ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2027 የሚዘጋጀውን ጉባኤ እንድታስተናግድ ተመርጣለች፡፡

ይህ አለም አቀፍ ጉባኤ በፀረ-አበረታች ቅመሞች እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ አንድምታ ያለው ኩነት ሲሆን ቀደም ሲል እ.ኤ.አ በ2018 በቻይና ቤጂንግ፣ በ2022 በአውስትራሊያ ሲድኒ እንዲሁም በ2024 በፈረንሳይ ተካሂዷል፡፡ በቅርቡ በፈረንሳይ በተካሄደው ጉባኤ ላይም አለም አቀፍ ተቋማትን ጨምሮ ከሁሉም የአለም አገራት የተወጣጡ 400 ተወካዮች ተሳትፈውበታል፡፡

የአለም አቀፉ የፀረ-ዶፒንግ የትምህርት ጉባኤ (Global Education Conference) በአፍሪካ ደረጃ ሲካሄድ ይህ የመጀመሪያ ነው፡፡ ስለሆነም ለአገራችን ገፅታ ግንባታ እና የቱሪዝም እድገት ከሚያበረክተው አስተዋፅኦ በተጨማሪ በአህጉር አቀፍ ደረጃ የፀረ-አበረታች ቅመሞች እንቅስቃሴውን የበለጠ በማጎልበትና ንፁህ ስፖርትን በማስፋፋት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ አገራችን ኢትዮጵያ አበረታች ቅመሞችን ወይም ዶፒንግን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በመደበኛ የትምህርት ስርዓት ውስጥ አካትቶ መተግበርን፣ በቂ የህግ ማዕቀፎችን በማውጣት ተግባራዊ ማድረግን፣ ጠንካራ የምርመራና ቁጥጥር ስርዓት መዘርጋትና ተግባራዊ ማድረግን ጨምሮ የተመዘገቡ በርካታ ውጤቶችን ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በአግባቡ ለማስገንዘብ ተጨማሪ እድል ይፈጥራል፡፡


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *